የኢትዮጵያ የሕብረተስብ ጤና ኢንስቲትዩት የአንድ መቶ አመት የአልማዝ ኢዩቤልዩ ክብረ በዓል የማስጀመሪያ መርሀ ግብር ፕሮግራም በዛሬ እለት በተቋሙ የስብሰባ አዳራሽ የተከናወነ ሲሆን ለበዓሉ የተዘጋጀው ልዩ የመረጃ ድህረ-ገጽ እና ተመራማሪዎች የምርምርና የጥናት ጽሑፎቻቸውን የሚያቀርቡበት፣ የሚገመገምበትና ውጤቱን የሚያሳወቅ ኢንስቲትዩቱ ያለማው የበየነ መረብ ስርዓት ይፋ ሆነዋል፡፡
ዶ/ር መሳይ ኃይሉ የኢትዮጵያ የሕብረተስብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በፕሮግራሙ ማስጀመሪያ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢንስቲትዩቱ ላለፉት አንድ መቶ ዓመታት በርካታ የሕብረተስብ ጤናን የተመለከቱ ጥናትና ምርምሮችን፣ የላብራቶሪ አገልግሎቶችን፣ የማሕበረሰብ ጤና አደጋዎችን የመከላከልና የመቆጣጠር ስራዎችንና እና ሌሎች ተያያዥ ተልዕኮዎችን ሲወጣ የነበረ በመወጣት ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ተቋሙ የሥራ አድማሱን በማስፋት በሀገር አቀፍ ደረጃ ልዩ ልዩ የሕብረተሰብ ጤና ነክ ስራዎችን በስፋትና በጥራት እንዲሁም በቅንጅት እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን ተቋሙ በአፍሪካ ቀዳሚ የሕብረተሰብ ጤና ተቋም ለመሆን እየሰራ ይገኛል።
ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም ላለፋት 1ዐዐ አመታት ኢንስቲትዩቱ የሀገሪቷ የሕብረተሰብ ጤና ጉዳዮች ምሶሶና ማዕከል በመሆን የሚጠበቅበትን አስተዋፅኦ ሲያበረክት እንደነበረ አውስተው አሁንም ቢሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን በመቆጣጠር፤ ጥራቱን የጠበቀ የላብራቶሪ አገልግሎት በመስጠት፣ በሕብረተሰብ ጤናና በስነ-ምግብ ዙሪያ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ ፣ በጤና ነክ መረጃዎች ትንተናና ቅመራ ዙሪያ እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ ሁሉን አቀፍ የአንድ ጤና እና የአለም አቀፍ የጤና ደህንነት መርሐ ግብር በማስተባበርና በመምራት ብሎም የኢፒዲሞሎጂን ስልጠናዎችን እና ሊሎች ተያያዥ የሆኑ የሕብረተሰብ ጤና ነክ የሆኑ ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
ኘሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ የአርመር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው የኢትዮጵያ የሕብረተስብ ጤና ኢንስቲትዩት ላለፋት 1ዐዐ ዓመታት በሕብረተሰብ ጤና ዙርያ ላደረገው ስራዎች ምስጋናቸውን አቅርበው ሁለቱ የምርምር ተቋማት ቀደም ሲል ሲያደርጉ እንደነበረው በቀጣይም በጋራና በሕብረት በመተባበር ስራቸውን እንደሚያከናውኑ የተቋማቸውን አጋርነት አረጋግጠዋል፡፡
ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ ኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር ስለ ኢንስቲትዩቱ የ1ዐዐ ዓመት ታሪክ፣ ስለ በአሉ አከባበር እንዲሁም ከአጋር አካላት ጋር ስለሚከናወኑ ቀጣይ ስራዎች ሰፋ ያለ ገለፃ አድርገዋል፡፡
በዚህ የክብረ ዕዓል ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የተለያዩ የመንግሥት እና መንግስታዊ ያልሆኑ እንዲሁም አጋር ድርጅቶች ታድመዋል።