You are currently viewing የሕብተሰብ ጤና ስጋት ተግባቦትና የሕብረተሰብ ተሳትፎ ላይ ያተኮረ ስልጠና ለሚዲያ ባለሙያዎች ተሰጠ

የሕብተሰብ ጤና ስጋት ተግባቦትና የሕብረተሰብ ተሳትፎ ላይ ያተኮረ ስልጠና ለሚዲያ ባለሙያዎች ተሰጠ

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ሚኔስቴር ጋር በመተባበር የወባ ወረርሽኝን ለመከላከላና ለመቆጣጠር በሚደረገው ቅንጅታዊ ስራ ሕብረተሰቡ ስለ ወባ መከላከያና የማጥፊያ መንገዶች ያለውን የግንዛቤ ደረጃ ከፍ ለማድረግ የሕብተሰብ ጤና ስጋት ተግባቦትና የሕብረተሰብ ተሳትፎ ላይ ያተኮረ ስልጠና ለመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች ሰኔ 28/2016 ዓ.ም በኢንስቲትዩቱ ስልጠና ተሰጠ፡፡
ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና እንስቲትዩት ም/ል ዋና ዳይሬክተር የወባን ወረርሽኝ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራን በተመለከተ ኢንስቲትዩቱ ከጤና ሚኒስቴር እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ከፍተኛ ስራ እየሰራ መሀኑን ጠቁመው የወባን መከላከያ እና መቆጣጠሪያ መንገዶችን በዝርዝር ለሚደያ ባለሙያዎች አቅርበው ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲፈጥሩም ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡ በሌላ በኩል ም/ዋና ዳይሬክተሩ የኢንስቲትዩቱን የመቶኛ ዓመት አከባበር ስነ-ስርዓት እና የተቋሙን አመሰራረት አሰመልክቶ ስልጠናውን ለታደሙት የሚዲያ አካላት አስረድተዋል፡፡
ዶ/ር ሕይወት ሰለሞን በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ ስራ አስፈጻሚ በስልጠና ፕሮግራሙ ላይ እንደገለጹት አሁን ካለንበት ዘመናት ቀደም ሲል በብዙ ሚለዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በወባ ከመያዛቸውም በላይ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ህይወታቸው ያልፍ ነበር፡፡ ነግር ግን በአሁኑ ሰዓት በዓለምም እንደ ሃገራችንም በመከላከሉና በመቆጣጠሩ ረገድ ጠንካራ ስራዎች በመስራታቸው በወረርሽኙ የሚጠቁ ብሎም የሚሞቱት በእጅጉ ከመቀነሱም በላይ መቆጣጠር ተችሏል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ሕይወት አያይዘውም በአሁኑ ሰዓት የወባ ወረርሽኝ በአገራችን በተለያዩ ቦታዎች የማንስራራት ሁኔታዎች እየታዩ እና ሰዎች በወረርሽኙ እየተያዙ በመሆኑ ሁሉም ባለድረሻ አካላት በቅንጅት ከፍተኛ ስራዎችን መሰራት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ በተለይም የሚዲያ አካላት ሕብረተሰቡን የመከላከያ እና የመቆጣጠሪያ መንገዶቹን በማስተማርና ግንዛቤ በማስጨበጥ በኩል ከፍተኛ ድርሻ ስላላቸው ከሚዲያ ባለሙያዎች ጋር በስልጠና የተደገፈ የውይይት መድረክ አዘጋጅተናል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
የወባ ወረርሽኝን በመከላከላና በመቆጣጠሩ ረገድ የሕብረተሰቡን ግንዛቤ ከፍ ለማድረግ የሕብተሰብ ጤና ስጋት ተግባቦትና የማህበረሰብ ተሳትፎ ላይ ያተኮረ ስልጠና በተለያዩ ባለሙያዎች ለሚዲያ ባለሙያዎች የተሰጠ ሲሆን በቀረበው ስልጠና መሰረት የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ውይይት በማድረግ በቀጣይ በሚደረጉ የመከላከል እና የመቆጣጠር ስራዎችን አስመልክቶ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡